ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት

ሪፖርተር ፡ ነአምን አሸናፊ

የኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ፣

የነሐሴ ወር ከማለቁ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባትና የዕርቅ ጉባዔ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ኮሚቴው ይኼንን ያስታወቀው ሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በራስ ሆቴል በሰጠው መግለጫ ሲሆን፣ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ የኮሚቴው የአገር ውስጥ ተወካዮች ናቸው፡፡

ኮሚቴው ከዚህ ቀደም በአሜሪካ በተለያዩ ግለሰቦች፣ የሲቪክ ተቋማትና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አማካይነት የተቋቋመ ነው፡፡

ከአገር ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ)፣

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እና የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኦሕዴኅ) የኮሚቴው አባላት ናቸው፡፡

‹‹የአገራችን ወቅታዊ ችግሮችና መፃዒ ዕድሎችን ለመወሰን ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ብቸኛ አማራጭ ነው፤›› የሚለው የኮሚቴው መግለጫ፣

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጨምሮ በአገር ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ የአገሪቱን የቆየ ችግር በማስወገድ

የተረጋጋች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት አስተዋፅኦ ለማድረግ በተዘጋጀው የብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ጉባዔ ቅድመ ዝግጅት መድረኮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአገሪቱን ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት እንደ መፍትሔ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች፣

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዕውን መሆን አንኳር የሆነውን ይቅርታ፣ የመፈቃቀር፣ የመግባባትና የመደመር ሕዝባዊ ጥሪ አካታች ሆኖ ማግኘቱን ኮሚቴው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

‹‹የአገራችን መፃዒ ዕድል ስኬታማ ይሆን ዘንድ በሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ፣ ባለድርሻ አካላት የሆናችሁ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች፣

የሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ ታዋቂ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የተረጋጋች፣

ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት ግፊት ለማድረግ በተዘጋጀው የብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ላይ እንድትሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን፤›› ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡና ተቋማት በጉባዔው ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here