#Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን) ፌስቡክ ገጽ ቤተሰብ ሳራ ይስሃቅ ጋር ተገናገኘን፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት አውቃት ነበር፡፡

ስኒ ቡና ይዘን – ስለአገር እና ሕዝብ አወጋን፤ ጨዋታችን በእንባ የራሰ ነበር፡፡

(የአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት በእንባ የራስ መልእክት … ይህ ነው)

በሃገሬ እያደገ ያለውን ዘረኝነት ሳሰብ ነብሴ የምትቆምበት ታጣለች፡፡ እኔ የተወለድኩት ከትግሬ  ኣባት፣ ኦሮሞ/ኣማራ እናት ነው፡፡

እድሜዬ ለትምህርት እስኪደርስ እድገቴ ከአያቴና ቅድመ አያቴ እቅፍ በኦሮሚያ ምድር ነዉ፡፡ አፍ መፍቻ ቋንቋያዬ አማርኛ እና ኦሮሚኛ ቢሆንም  ትግርኛ ቋንቋ  እናገራለሁ፡፡

ከአንደኛ እሰከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማርኩት በዉቢቷ ሐዋሳ ነዉ፡፡ እህት እና አራት ወንድሞች አሉኝ፡፡  ከአባቴ የሚወለደው ወንድሜ ከጎንደሬ እናቱ ተዎልዶ ጎንደር ምድር ነው ያደገዉ::

ጌጣችን … እንደምታውቀው የኮንሶን ምድር እና ሕዝብ የማኅበረሰቡ ያህል በደንብ ታውቀዋለህ፡፡

እኔ – በሥራ አጋጣሚ ከኮንሶ ማኅበረሰብ ጋር በነበረኝ መቀራረብ የባህላዊው መሪው ጎሳ /ከላ ጎሳ/ በባህላዊ ሥነስርዓት የማህበረሰቡ አባልነትን ክብር አኣዲስ ስያሜ ጋር /ከሌ/ በታላቅ ድግስ ተበረከተልኝ::

በኮንስኛ ተነሳሁ፤ ሳራ ሥሜ ቀርቶ ‹‹ከሌ›› ተባልኩ፤ የኮንሶማኅበረሰብ ሆንኩ:: እህታቸው ሆንኩ፡፡ እነርሱም ከእህታቸው፤ እኔም ከወንድሞቼ ጋር መጋባት አምችልም፡፡

የእግዚአብሔር በረከት በዝቶልኝ ሁለት ድንቅ ልጆች ከሶዶ /ወላይታ/ ምድር አገኘሁ።አንዱዋን ወለድኩ፤ አንዱዋን በጉዲፈቻ ወሰድኩ፡፡

ልጆቼ – አዲስ ኣበባ ኣደጉ፡፡ አሁን 10 እና 15 ዓመት ሆነዋል::

እናም ጌጣችን … አሁን ያለው የዘረኝነት በሽታ እኔን ከትግሬው አባቴ፡ከኦሮሞዋ እናቴ ወይስ ከጎንደሬው/ አማራው ወንድሜ ወይስ በፍቅር እጃቸውን ዘርግተው የኮንሶ ማኅበረሰብ አባል ካደረጉኝ ኮንሶዎች

፣ከወላይታዎቹ ድንቅ ስጦታዎቼ /ልጆቼ/ ፣ ከውቢቱዋ የእድገት አገሬና የቤተሰቦቼ መኖሪያ /ከ25 ዓመት በላይ/ ሐዋሳ ወይስ ከልጆቼ የትውልድ አገር አዲስ አበባ ከየት ወግኖ ያቆመኝ ይሆን?

እኔ – ወገንተኝነቴ ለአገር እና ለሕዝብ፤ ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ምርጫ የለኝም፡፡

ጌጣችን … የአባትን ፍቅርታውቃለህ – አባቴ ይስሃቅ ተክሉ መሸሻ የወላድ መካን እንዲሆን አልፈልግም፡፡ አባቴ በዘሩ እንዲገለል አልፈልግም፡፡

አባቴ በኢትዮጵያዊነት የቆመ ነው፡፡ አባቴን በዘሩን አትዩብኝ፡፡ ለኔ አባቴ ሁሉ ነገሬ ነው፡፡ ስለዚህም እኔ ልጁ፤ ሳራ ከአባቴጎን ትናንት እና ዛሬ ቆሚያለሁ፤ ነገም አብሬው እቆማለሁ።

እናቴ፤ ጥሩነሽ ዘርፉ ደሳለኝ የዘጠኝ ወር ቤቴ ናት፡፡ እርሷም በፍጹም  የወላድ መካን አትሆንም፡፡ እባካችሁ የእናቴን ዘር አትዩብኝ፡፡ እናቴ ለኔ ሁሉ ነገሬ ናት፡፡ ሰለዚህ አብሬያት እቆማለሁ።ጉያዋ፤ እቅፏ ይሞቀኛል፡፡

ይህ የአባት፣ የእናት እና የልጅ የደም፣ የፍቅር ሰንሰለት አይበጠስም፡፡

ይህንን ተፈጥሯዊ ሰንሰለት ለመበጠስ የሚታገል ሰው አልፈቅድም፡፡

ጌጣችን … ወንድሜን፤ ያባቴን ልጅ ወንድሜ መከታዬነው፡፡ ወንድሜን ዘርህ ምንድነው አይበሉብኝ፡፡

ወንድሜ ከአንተም ጋር እኔ እህትህ አብሬ እቆማለሁ፡፡ የወንድሜን  ክፉ የሚያይ አንጀት የለኝም

ጌጣችን … ልጆቼ የኔ ውድ ስጦታዎች፤ መልኮቼ ናቸው፡፡ ከእነርሱ በፊት እኔን ያርገኝ፡፡ እባክህ፣ እባክህ ልጆቼን ብሔራችሁ  ምንድነው አይበሉብኝ፡፡

እኔ እማውቀው ከጨቅላነት እሰከ እውቀት ያለውን የእናት እና የልጅ ፍቅር ብቻ ነው፡ይሄ እንዴት ይቆረጣል …. ከልጆቼ ጎን እቆማለሁ፡፡

//… ያዘዝነው ስኒ ቡና አልተጠጣም! //

በመጨረሻም… በፍቅር ወቅት እጃችቸውን ዘርግተው፤ ልጃችን ብለው የተቀበሉኝን የታታሪነት ተምሳሌት የሆኑት የኮንሶ ሕዝብ ዛሬ በዚህ ወቅት ፊቴን የማዞርበት አቅም የለኝም፡፡

አዎ ጠንካሮቹ፤ ሥራ ወዳዶቹ የኮንሶሕዝብ ጋር እቆማለሁ።

በልዩ የልጅነት ትዝታ ውጤን ያስዋብሺው ውቢቱ ሐዋሳ ካንቺም ጋ እቆማለሁ የልጆቼ ቤት አዱ ገነት ካንቺም ጋ እቆማለሁ ።

አዎ ማንንም መተው አልችልም ሁሉም ጋ በአንዴ መድረስ አልችልም፡፡ መምረጥም አልችልም፡፡

ጌጣችን … (አንተ የምትጠቀምባትን ቃል ልዋስህና – እናንት ያገሬ ልጆች …) እባካችሁ ነብሴ ተጨነቀች፡፡

ፈውሴ አንድና አንድ ነው – ኢትዮጰያዊነት። አዎ ስንቶቻቹ በኔ ጫማ ቆማችሁ ይሆን ?

ይህንን ታሪክ ሼር በማድረግ ለአገር እና ለህዝብ አድርሱ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here