ከባሕር ወለል በላይ በ2300 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው እጅግ አስገራሚው የአቡነ ይምዓታ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ!

ጥቅምት 28 ቀን በዓመታዊ የዕረፍታቸው በዓል ታስበው የሚውሉት አቡነ ይምዓታ ይህንን ተራራ በተአምራት በፈረስ እንደወጡት ገድላቸውን ጠቅሰው የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ፡፡

ከአገልጋዮቻቸው አንደኛው ለፈረሱ ራት ሳር ሳይሰጠው በውሸት “ለፈረሱ ሳር ሰጥቼዋለሁ” ብሎ አቡነ ይምዓታን ይዋሻቸዋል፡፡

እርሳቸውም የተሰወረውን ሁሉ ያውቁ ነበርና “…ውሻ እንጂ የሰው ልጅ በሐሰት አይጮህም” ብለው ሐሰትን ስለመናገሩ ገሠጹት፣ ወዲያውም በተአምራት ከአንገቱ በላይ የውሻ መልክ ያለው ሆነ፡፡

የአቡነ ይምዓታ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ ትግራይ ገርዓልታ ልዩ ስሙ ‹‹ጎሕ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይገኛል፡፡

ቤተ መቅደሱ ሰማይን እንደ ምሰሶ ደግፈው የያዙ የሚመስሉ በጣም ረጃጅም ተራሮች መካከል በአንደኛው ጭፍ ላይ ይገኛል፡፡

ቤተ መቅደሱ ከባሕር ወለል በላይ በ2300 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ያለበት የተራራው ርዝመት ብቻውን 300 ሜትር ነው፡፡

ቤተ መቅደሱ በር ላይ ለመድረስ በጭንቅና በፍርሃት ሆኖ ተራራውን እንደዝንጀሮ በእጅ እየቧጠጡ መውጣት ይጠይቃል፡፡

እርሱም ቢሆን በገዳሙ አባቶች እገዛና ድጋፍ ካልሆነ መውጣት የማይቻል ነው፡፡

ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚደንቀው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ብቻ አይደለም ውስጡ ያሉት የግድግዳ ላይ ሥዕሎችም በ6ኛው መ/ክ/ዘመን የተሣሉ እጅግ ድንቅና ጥንታዊ ናቸው፡፡

ስለዚሁ የአቡነ ይምዓታ እጅግ አስደናቂ ቤተ መቅደስ ገድለ አቡነ አረጋዊ ‹‹በሞት በዐረፉ ጊዜ የሥጋቸው ሥርዓተ ግንዘት በመላእክት እጅ ነው የተከናወነው፡፡

ይልቁንም ቁመቱና ርዝመቱ ከታላላቅ ገደል እጅግ በጣም የሚበልጥ የድንጋይ ዓምድ ከወንዝ ማዶ ዘንበል ብሎ መጥቶ ሥጋቸውን በክብር ተቀብሎ

በተራራው ጫፍ ላይ እስከዛሬም ድረስ ፈጽሞ ሳይነቃነቅና ሳይናወፅ ቀጥ ብሎ ቆሞ ይገኛል›› በማለት ይገልጻል፡፡

የአቡነ ይምዓታ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here