– ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል አሳሰበ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተመደቡ አዳዲስ የቦርድ አባላትን ሹመት በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 113/1987 አንቀጽ 7 መሰረት የድርጅቱ አዳዲስ የቦርድ አባላት ሹመት ጸድቋል፡፡

የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 8/2010 መሰረት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚዲያ ልማትና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አያሌው  የቦርድ ሰብሳቢ፣በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፣በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረዳት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ተሻገር ሽፈራው እና ዶክተር ዮሐንስ ሽፈራው በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ ሹመቱን አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ምክር ቤቱ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን የ8 ወራት አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን፤  በአገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመቀነስና ወጣቱን ወደ ሥራ ለማሰማራት የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በተለይም በግብርና ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ወጣቶች ያለው የብድር አሰጣጥ ሥርዓት ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት በመሆኑና የወጣቱን ችግር በአግባቡ እየፈታ ባለመሆኑ መስተካከል እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

የምክር ቤቱ አባል አቶ ጌታቸው መለስ፤ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ሥራ ላይ እያዋለ አለመሆኑንና እንዲያውም ተዘዋዋሪ ፈንድ መሆኑ ቀርቶ መደበኛ ብድር እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

በተለይ ወጣቶች ከተደራጁ በኋላ በብድር አሰጣጡ ምክንያት አተገባበሩ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን፤ በገጠር አካባቢ ያሉ ወጣቶች የቤተሰባቸውን መሬት በዋስትና እንዲያሲዙ እየተጠየቁ ነው፡፡

ይህም ወጣቱ ተደራጅቶ መስራት እንዳይችል ከማድረጉ ባሻገር የተደራጁ ወጣቶች እንዲበተኑ፣ ሥራ አጥነት እንዲበራከት በማድረጉ ተዘዋዋሪ ፈንዱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል አድርጓል ብለዋል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ዕርስቱ ይርዳው፤ የወጣቶችን ችግር ለመቅረፍ በተሰሩ ሥራዎች ውጤቶች ቢመዘገቡም ከችግሩ ስፋት አኳያ በቂ ሥራ አልተሰራም፡፡

በተለይ ከተዘዋዋሪ ፈንድ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከብድር ስርጭት ጋር በተያያዘ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ሲሆን፤ አመራሩ በወቅታዊ አገራዊ ሥራዎች መጠመዱ፣ የአስፈጻሚ አካላት ቅንጅት አናሳ መሆን፣ በመስሪያና መሸጫ ቦታ አቅርቦት መዘግየት፣ የተዘዋዋሪ ፈንድ ለማስተዳደር ከወጣው መመሪያ ውጭ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥና ፈንዱ በፍጥነት ሥራ ላይ አለመዋሉ ለችግሮች መንስኤ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ሊወጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ዑመር እንድሪስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here