(ኤፍ ቢ ሲ) የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ለቀድሞው የሃገሪቱ መሪ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤ ያለመከሰስ መብት መተማመኛ አልሰጠሁም አሉ።

ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ለቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤት ያለመከሰስ መብት አለመስጠታቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በስዊዘርላንዷ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፥ ለቀድሞው የሃገሪቱ መሪ ለእርሳቸው በሚበጅ መልኩ ከስልጣን እንዲወርዱ ሃሳብ ማቅረባቸውን ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈም ሙጋቤ ስልጣን የሚለቁ ከሆነ እርሳቸውና ቤተሰባቸው በሃገራቸው በሰላም እንደሚኖሩ ማረጋገጫ እንደሚሰጧቸው መግለጻቸውንም ሄራልድ የተሰኘው የሃገሪቱን ጋዜጣ ጠቅሶ ሺንዋ ዘግቧል።

ከዚህ ባለፈ ግን ለማንኛውም ወገን ቢሆን ያለመከሰስ መብትን በተመለከተ መተማመኛ አልሰጠሁም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የቀድሞ ስልጣንና ሃላፊነት የሃገሪቱ ፖሊስ ተፈጽሟል ብሎ ከጠረጠረው ወንጀል ጋር በተያያዘ ሊያደርግ ያሰበውን ማጣራትም ሆነ ምርመራ ለማስቆም ዋስትና እንደማይሆን ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንቱ በቃለ መጠይቃቸው ሙጋቤና ቤተሰቦቻቸው በሰላምና ደህንነት የሚኖሩበትን አግባብ ለማመቻቸትና ለማረጋገጥ የእርሳቸው አስተዳደር ማንኛውንም ነገር ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣዩ ክረምት ከሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘም፥ በምርጫው ማንኛውንም አይነት ውጤት እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

በሙጋቤ የስልጣን ዘመን ከታዛቢነት የተከለከሉት እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ ተቋማትም፥ የክረምቱን ምርጫ በዚምባቡዌ ምድር መታዘብ ይችላሉም ነው ያሉት።

የምርጫውን ቀን በተመለከተም በቀጣዩ ወር ከሚጠናቀቀው የመራጮች ምዝገባ በኋላ ይፋ እንደሚያደርጉአስረድተዋል።

ሃገራቸው ከአለም አፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር ትሻለች ያሉት ምናንጋግዋ፥ እንደ አሜሪካ ያሉ ሃገራት በሃገራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ቢመጡ እንደሚቀበሉም ጠቁመዋል።

ምናንጋግዋ ባለፈው ህዳር ወር ከቀድሞው የሃገሪቱ መሪ ሮበርት ሙጋቤ መንበረ ስልጣኑን መረከባቸው ይታወሳል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here