የጡት ካንሰር በሽታ ምንድን ነው?

የጡት ካንሰር በአብዛኛው በሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን ወንዶችንም የሚያጠቃ የካንሰር ዓይነት ነው፡፡

ካንሰር ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህመም አይነቶች አጠቃላይ መጠሪያ ስም ነው፡፡
በሽታው ከሌሎች በሽታዎች ተለይቶ የሚታወቀው ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ማደጉና ሴሎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመውረር በመቻሉ ነው፡፡
የጡት ካንሰርም በቅድሚያ በጡት ላይ በመከሰት በሽታው በአጭር ጊዜ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመዛመት የከፋ ችግር ሊያስከትል የሚችል በሽታ ነው፡፡

ጡት በተፈጥሮ በውስጡ ወተት ለማመንጨት የሚያስችሉ በርካታ ከረጢት መሰል ነገሮች እንዲሁም እነዚህን ከጡት ጫፍ ጋር የሚያገናኙ ቱቦዎች አሉት፡፡

እነዚህ ቱቦዎች በእርግዝና ወቅት ወተት ለማመንጨት ትልቅ ሚናን የሚጫወቱ ናቸው፡፡
የጡት ካንሰር በአብዛኛው ማደግ የሚጀምረው በእነዚህ ቱቦዎች ውስጥ ነው፡፡
የጡት ካንሰር ተፈጠረ የሚባለው አንድ ጤነኛ ያልሆነ ህዋስ በሰውነታችን ውስጥ ተፈጥሮ ከገደብ በላይ መራባት ሲጀምር ነው፡፡
የተራባው ህዋስም በጊዜ ሂደት ጤነኛ የነበሩ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ህብረ ህዋሳትን በማጥቃት በሽተኛ ያደርጋቸዋል፡፡

ለጡት ካንሰር የሚጋለጡት እነማን ናቸው?

የጡት ካንሰር በብዛት ሴቶችን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን የሚመጣበት ምክንያት በውል አይታወቅም፡፡

የሚከተሉት ግን የበለጠ ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነዚህም፡-
• ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች፣
• ከዘር/ ከቤተሰብ በጡት ካንሰር የተያዘ ካለ፣
• ካንሰር ያልሆኑ ሌሎች የጡት በሽታዎች አጋጥሞ ከነበረ፣
• የአልኮል መጠጥ የሚያበዙ፣
• ያዩ፣
• ከ30 ዓመት በኋላ ልጅ የሚወልዱ ወይም ከነጭራሹ የማይወልዱ፣
• ከሚገባው ዕድሜ በጣም ዘግይተው ያረጡ፣
• ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ የሚያዘወትሩና ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው እንዲሁም

• በከፍተኛ ጨረር ውስጥ ያለምንም መከላከያ የሚሰሩ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡

የጡት ካንሰር ምልክቶች

የጡት ካንሰር ሲጀምር ህመምም ሆነ ምልክቶች የሉትም አብዛኞቹ የጡት እብጠቶች ካንሰር ባይሆኑም ዋነኛው የጡት ካንሰር ምልክት ግን በጡት ላይ የሚከሰት ጠጣር እብጠት ሲሆን የሚከተሉት ደግሞ ተጨማሪ ምልክቶች ናቸው፡፡

ከጡት ጫፍ ደም የቀላቀለ ፈሳሽ መውጣት፣ የጡት ጫፍ አካባቢዎች መቅላትና ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ በጡት አካባቢና በብብት ውስጥ እብጠት መከሰትና ሙቀት ያለው መሆን፣ የጡት ቆዳ መሸብሸ/ወደ ውስጥ መግባት ወይም እንደብርቱካን ልጣጭም ዓይን ማውጣት የሚሉት በዋነኝነት ይገኙበታል፡፡
ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራና ህክምና ማድረግ ይገባል፡፡
የራስን ጡት በራስ የመመርመር ዘዴ

የራስ በራስ የጡት ምርመራ በየወሩ ማድረግ ህይወትን ከሞት ለመታደግ ያስችላል፡፡

ጡት በወር አበባ ምክንያት በቅርጽ፣ በመጠንና በስሜት ስለሚቀያየር ሁልጊዜ በየወሩ በተለመደ ቀን መመርመር አለበት፡፡
ይህን ማድረግ ጡት ላይ የሚከሰት ማንኛውንም ለውጥ ለማወቅ ይረዳል፡፡
ዋና ዋናዎቹ የራስ በራስ የጡት ካንሰር ምርመራ ዘዴዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ምስል 1:- በመስተዋት ፊት በመቆም ከወገብ በላይ በማውለቅ እጅን ጎን ላይ በማድረግና ቀጥ ብሎ በመቆም በሁለቱም ጡቶች ላይ ያሉትን ለውጦች መከታተል፤

ምስል 2:- ሁለቱንም እጆች በጭንቅላት ትክክል ከፍ አድረጎ በመያዝ ከላይ የተዘረዘሩት ዓይነት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ ማስተዋል፣

ምስል 3:- አንደኛውን እጅ ከጭንቅላት በላይ ከፍ በማድረግና በሌላኛው እጅ ደግሞ በተቃራኒው ያለውን ጡት በመዳሰስ ጠጣር ነገር መኖሩን ማረጋገጥ፣

በጀርባ በመተኛት አንደኛውን እጅ በመንተራስ በሌላኛው እጅ በተቃራኒው ያለውን ጡቱ በመጀመሪያ ዙሪያውን፣ ቀጥሎም የላይኛውን ክፍልና በመጨረሻ የጡት ጭራ የሚባለውን ብብት ውስጥ በመግባትና በመዳበስ የጓጎለ ነገርና እብጠት መኖሩን መመርመር፡፡
.
#መከላከያ_ዘዴዎቹ፡-

የስውነት ክብደት መቆጣጠር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ የአመጋገብ ስርአት መከተል፣ ጡት ማጥባት፣ ትምባሆ አላማጨስ፣ አልኮል አለመጠጣት፣ እንዲሁም ሆርሞኖችን ረጅም ጊዜ አለመውሰድ የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

Ministry of Health,Ethiopia

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here