(ኤፍሬም እንዳለ)

ስፍራው ያው ቦሌ ነው፡፡ ቤተመንግሥት ሊመስል ምንም ያህል አይቀረው የሚባል ግቢና ቤት፡፡ ቦሌዎች መሆናቸው በሚያስታውቁ ሰዎች ተሞልቷል፡፡ ድግስ ነበር … የባለቤቶቹ ልጅ በሆነ ነገር ተመርቃ እሱን ለማክበር የተዘጋጀ ነው፡፡

ምግቡ፣ መጠጡ ተትረፍርፏል፡፡ እዚሁ ላይ በአጋጣሚ የተጋበዘ የቦሌ ያልሆነ ሰው ነበር፡፡ እናም፣ “እንዴት አንዲት ልጅ ተመረቀች ተብሎ ሦስት ድል ያለ ሰርግ የሚወጣው ድግስ ይደገሳል!” እያለ ይገረማል፡፡ ለክፉም ለደጉም የተመረቀችበትን ለማወቅ አንዱን ተጋባዥ ይጠይቀዋል፡፡

“ለመሆኑ በምንድነው የተመረቀችው?” ይለዋል፡፡ መልሱንም ያገኛል፡፡ ለካስ ልጅቱ ከሆነ የልብስ ቅድ ትምህርት ቤት የሦስት ወር የስፌት ምናምን ኮርስ ወስዳ ሰርተፊኬት ሰጥተዋት ነው፡፡ እንግዲህ ያለው ማማሩ አይነት ነገር ነው፡፡

ሰሞኑን ከምንሰማው “ጉድ!” የሚያሰኝ ዜና ቢያንስ የእሷ ይሻላል፡፡ ሦስት ቀንም ሆነ ሦስት ወር ኮርሷን ወስዳ ነው የተመረቀችው፣ ሰርተፊኬቷ በ‘ፎርጀሪ’ የተሠራ አይደለም፡፡

በዛ ሰሞን የተለያዩ ክልሎች “በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሥራ የተቀጠራችሁና እድገት ያገኛችሁ ራሳችሁን አጋልጡ” ሲባል፣ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የአዲስ አበባ ተራ ደረሰ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማይመጥናቸው ሥራ ላይ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው ተብሏል፡፡ ያውም በመንግሥታዊ መዋቅሩ ስር ብቻ፡፡ በሺዎች ! እንደገናም ተገርመን እንላለን … በሺዎች!

እንዲህ አይነት ዜና እንዴት ነው ምድርን መንቀነቁ የቀረው ! እንዴት ነው ይህን ያህል “የራሳቸው ጉዳይ!” አይነት ባህሪ የገነነው ! ለመሆኑ በኔይማር የቁርጭምጭሚት ጉዳት ፍራሽ አንጥፋችሁ ሊለን ምንም የማይቀረው ሚዲያ ምነው ልሳኑ ተሸበሸበሳ!

ከሁለት ቀናት በፊት በኦሮሚያ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሠሩ የነበሩ ስድስት ሺሀ ሰባት መቶ የመንግሥት ሠራተኞች ራሳቸውን ማጋለጣቸውን በዜና ተነግሯል፡፡ እንዲሁም ከአራት ሺህ ባለይ በሀሰተኛ ማስረጃ የተቀጠሩ ተደርሶባቸው ተብሏል፡፡ ብዙ ነው፣ እጅግ ብዙ ነው፡፡

ለምሳሌ ህክምና አለ፡፡ ሲያስቡት ያስፈራል፣ በጣም ያስፈራል፡፡ “የቱ ጋ ነው የሚሰማህ?” ምናምን እያሉ ከሚደባብሱን ሀኪሞች መሀል ስልጠናው የሌላቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰቡ ያስፈራል፡፡ መቀመጫችን ላይ መርፌ ከሚጠቀጥቁብን ነርሶች መሀል በእርግጥም ስልጠናው የሌላቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰቡ ያስፈራል፡፡ ለተከበረው የህክምና ሙያና ለተከበሩት ሙያተኞቹም አንገት ሊያስደፋ ይችላል፡፡ የሰው ልጅ ህይወት እንዲህ የረከሰበት ዘመን ! የህብረተሰብ አገልጋይነት እንዲህ ክብር ያጣበት ዘመን !

ዋናው ጥያቄ ግን የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ነገር ይህን ያህል ሲስፋፋ፣ አስራዎች አልፎ፡ መቶዎች አልፎ፣ ሺዎች ሲገባ፣ እዚህ አስደንጋጭ ደረጃ ሲደርስ ምነው በትንሹ ‘ኮሽ’ የሚል ነገር እንኳን አልነበረም ! ለነገሩ፣ አይደለም በየስርቻው የሚሠራውን ‘ፎርጀሪ፣’ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ‘ዲፕሎማ በዚህ ያህል ብር፣ ዲግሪ በዚህ ያህል ብር’ ይሸጣል የሚባሉ ተባራሪ ወሬዎች ስንሰማ ከርመናል – በወሬ አለፍነው እንጂ፣ መረጃ እንጂ ማስረጃ የለም እያልን ተቀላለድን እንጂ ስንሰማማ ከርመናል…

አሁን እንደምንሰማው ግን ምንም የሚያቀላልድ ነገር የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ የአገር ጉዳይ፣ የትውልድ ጉዳይ፣ የህብረተሰቡ የወደፊት እጣ ፈንታ ጉዳይ ነው፡፡ እንደምንሰማው ከሆነ ግን ነገሩ በወሬ ደረጃ ስንቀባበለው ከነበረውም የባሰ ነው፡፡ አሁንም ደግመን ተገርመን እንላለን … በሺዎች የሚቆጠሩ!

አይደለም የአገር ውስጥ የትምህርት ማስረጃዎችን ከውጪ በተልዕኮም ሆነ በምንም ተገኙ የተባሉትን የትምህርት ማስረጃዎችን “በዚህ ያህል ዶላር የተሸመቱ፣” “በዚሀ ያህል ፓውንድ የተገዙ” እያልን ‘ጠርጥር ከገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር’ ስንል ነበር፡፡ በአንዳንድ የሰለጠኑ ሀገራት ያሉ ‘ዲፕሎማ ፋክተሪ’ የሚባሉት ይሠራሉ የሚባሉትን ስንሰማ ደግሞ … ይህም የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡

በነገራችን ላይ አሜሪካ ውስጥ እውቅና የሌላቸው የሀሰት ዲግሪና ዲፕሎም የሚቸበችቡ ከሦስት መቶ በለይ ተቋማት አሉ ነው የሚበለው፡፡ ከእነሱ አንዳንዶቹ ወደ መቶ ከሚጠጉ ራሳቸው የብቃት ማረጋጋጫ የሌላቸው የብቃት ማረጋጫ ሰጪዎች ብቃት ማረጋጋጫ ተሰጥቷቸዋል፡፡

“ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ዲፕሎማዎችን በመሥራት እንደ ዲፕሎማ ካምፓኒ የተዋጣለት የለም፡፡ ምርቶቻችን በከፍተኛ ጥራት የታተሙ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ዲፕሎማዎች፣ የኮሌጅ ዲግሪዎች፣ ትራንስክሪፕቶችና በርካታ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ሰርተፊኬቶች ምርጫዎችን ያካትታል፡፡” በኢንተርኔት ላይ የተለቀቀ ማስታወቂያ ነው፡፡ “ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንሰጣለን” የሚሉ ማስታወቂያዎች የጉድ ናቸው፡፡

ብዙዎች ማስረጃዎች ደግሞ ኦንላይን ስለሚሸጡ ጨርቆስ ቁጭ ብሎ ከቺካጎ ማስላክ ይቻላል፡፡ ‘የሚፈልጉትን አይነት የኮሌጅ ዲግሪ በ24 ሰዓት !” በሀያ አራት ሰዓት ጥንቅቅ ለሚል ነገር ምን ሀያ አራት ዓመት አለፋችሁ አይነት ነው፡፡

በ2007 የወቅቱ የስዊድን የሥራ ሚኒስትር የነበሩት ሰው ፌይርፋክስ ዩኒቨርሲቲ ከሚባል የአሜሪካ ተቋም ኤምቢኤ ዲግሪ አለኝ አሉ፡፡ የተባለው ዩኒቨርሲቲ ግን ‘ዲፕሎማ ሚል’ ወይም ‘የዲፕሎማ ፋብሪካ’ ተብሎ ሰለሚታወቅ ወረቀታቸው በአገራቸው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሊያሳምኑ ሞክረው አለሆነላቸውም፡፡

እኛ አገር እንዲሀ አይነት ነገር ከፍ ባሉ ወንበሮች አካባቢ ላለመኖሩ ምን ማስተማመኛ አለን ! በቀደም የአዲስ አበባው ዜና ላይ በሀሰተኛ ማሰረጃው ጉዳይ አመራር ላይ ያሉ ስለመኖራቸው ጥቆማ መኖሩ ተነግሯል፡፡

አሁን ጥያቄው በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን ይህ እንዳይፈጠር የሚያደርግ ስርአት መዘርጋት ይህን ያህል ኩዋንተም ፊዚክስ የሚባለውን ያሀል ይከብዳል እንዴ! በኮምፒዩተር ዘመን፣ አንድ ሁለት ፐሮግራሞች በመፍጠር ማሰተካከል በሚቻልበት ዘመን እንዴት ነው በሺህ የሚቆጠሩ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ለማለት የደረስነው !

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ የሚያስመርቋችውን ተማሪዎች ዝርዝር ለሚቆጣጠራቸው ተቋም የሚያስተላፉበት አሠራር የለም እንዴ ! የሚመለከተው ተቋም አንድ የመረጃ ዌብ ሳይት ከፍቶ ቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች በቀላሉ የተመራቂዎችን እውነተኛነት ለማጣራት የሚያስችል ዘዴ ለመዘርጋት መቼም የአይንስታይንን አእምሮ ቆፍረን ማውጣት አይኖርብንም!

ጡቡን ከበርበሬ፣ ጄሶውን ከእንጀራ፣ ሙዙን ከቅቤ እየቀላቀሉ ይቸበችባሉ እያልን ስለማጭበርበር መረን መልቀቅ ስናወራ ኖረናል፡፡ የጅብና የአህያ ስጋ የከብት ሥጋ አስመስልው ሲሸጡ ሰለነበሩ ስናወራ ኖረናል፡፡ የሞቱ ዶሮዎችን እየበለቱ ለገበያ ያቀርቡ ነበር ስንል ከርመናል፡፡

ብዙ መኖሪያ ቤቶች ሲገባ ወይ የባለቤቶቹ፣ ወይ የልጆቻቸው በምረቃት ጋዋን የተነሷቸው ፎቶዎች ግድግዳዎች ላይ እናያለን፡፡ በቃ፣ ያ ሰው በሆነ ትምህርት ተመርቋል ማለት ነው፡፡ እንደ ሰሞኑ ወሬ ግን “ይቺ እንኳን የሽወዳ ፎቶ ነች!” እያልን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡ አንዳንድ ክርክሮች ላይ በፊት ለፊትም ይሁን በተዘዋዋሪ ማስረጃቸውን ከውጭ ይዘው የመጡትን “እሱ አኮ የውሸት ዶከተር ነው፣” ምናምን እየተባባሉ በነገር ሲወጋጉ እንሰማለን፡፡

ያሳዘናል፡፡ “ኸረ የትምህርት ጥራትን ማስተካከል ከማይቻልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት የሆነ ነገር ይደረግ!” እየተባለ በሚጮህበት ሰዓት ይሄ ሁሉ ሰው በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማይገባውን ቦታ መያዙ ለተመልካችስ ምን ይፈጥራል!

በባዶ ሜዳ “የመልካም ገጽታ ግንባታ” እየተባለ የሚለፈፈው “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን” ከሚለው መፈክር አይለይም፡፡ ተፈጥሮ በቁጥጥር ስር እንደማትውል በተደጋጋሚ እሳይታናለች !

እና እንደ ሀሰተኛ የትምህርት ማሰረጃ አገሪቱን ማጥለቅለቅ የመሰለ ገጽታ የሚያበላሽ ነገር ይኖር ይሆን ?

ነገራችን “እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽ፣” ሆኖ ያለን አልበቃ ብሎ፤ “ራሳችሁን አጋልጡ እንጂ ከዚህ በፊት የበላችሁትን ገንዘብ መልሱ አትባሉም” ምናምን የሚባል ነገርም አለ፡፡

በእርግጥም ይህን ያህል በተስፋፋ ነገርና ገና ጥልቀቱና ስፋቱ ባልለየ ነገር “እስከዛሬ የበላሃትን ትፋት!” አይነት ብዙም ወንዝ ላያሻግር ይችላል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ በስርአቱ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች “የእንጀራ ያለህ!” “የሥራ ያለህ!” እያሉ ለዓመታት በሚንከራተቱበት ጊዜ የእነሱ ቦታ በሀሰተኛ ማስረጃ በገቡ ሰዎች መያዙ ሊያሳስበን፣ ሊያስጨንቀን ይገባል፡፡ ጥያቄው የእውነት አስጨንቆናል ወይ፣ አሳስቦናል ወይ የሚል ነው፡፡

ግድግዳው ገና በጥቂት ወሩ የሚሰነጣጠቅ ኮንዶሚኒየም ስናይ እንጠራጠራለን፡፡ ኮንዶሚኒየምን የመሰለች እጅግ ዝቅተኛውን የግንባታ ጥበብ የምትጠይቅ ሥራ መሥራት ሲያቅተን “መጀማሪያስ ቢሆን ባለሙያ መች ሠራውና!” እንላለን፡፡ አንድ ሰሞን የግንባታው ፕሮጀክቶች “አቅማቸው ለማይፈቅድ ሰዎች እየተሰጠ” ምናምን ሲባል ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ለእንዲህም የሚያበቃን እኮ ልንደማመጥ አለመቻላችን ነው፡፡ አሁን፣ አሁንማ አይደለም መደማመጥ መነጋገርም እየተውን ነው፡፡ ብንነጋገር እንኳ ከንግግራችን ቁም ነገር መፈለግ ጠፍቷል፡፡ አንድ ነገር በተተነፈሰ ቁጥር “ኒኦ ሊበራል፣” “ኋላቀር” ምናምን እየተባለ ዝም፣ ጭጭ ለማሰኘት መሞከር ነው የተያዘው፡፡ ይቺ ኒኦሊበራል የሚሏት ነገርማ አንዳንዴ የሆነች ነገረኛ የሰፈር ሴት ልትመስል ምንም አይቀራት፡፡ የፖለቲከኛ ሁሉ አፍ ማሟሻ ሆናለቻ!

በነገራችን ላይ የዘንድሮዋ ‘ኒኦሊበራል’ የሚሏት ነገር እንደቀድሞው “የኢምፔሪያሊስቶች ቡችላ” የሚባለው አይነት ትርጉም አላት እንዴ!

የሚያሳዝነው ነገር፣ እኛ በበዙ ነገር ለመሸወድ ራሳችንን ዝግጁ አድርገን የምንጠብቅ ነው የሚመስለው፡፡ ዶክተር ኢንጂነር ሳሙኤል ዘሚካኤል፣ አይደለም እኛ ተራ ዜጎቹን ስንት በከፍተኛ ደረጃ የተስተማሩ ምሁራን የተሰበሰቡባቸውንና “እኛ ዘነድ ና!” “የለም እኛ ዘንድ ና!” እያሉ ሲሻሙበት የነበሩትን ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችን አሞኝቷቸዋል፣ በየአዳራሹ አስጨብጭቧቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአውስትራሊያ ከካንቤራ ዩኒቨርሲቲ፣ በአሜሪካ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪ መሰበሰቡን ሲናገር “በአንተ መጀን!” ብለን ነበር የተቀበልነው፡፡

ሰውየው ያልቀረበባቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ቢኖሩ ጥቂት ናቸው፡፡ “ፑቲን ጓደኛዬ ነው፣ በርካታ የዓለም መሪዎችን አግኝቻለሁ፡” አይነት የወዲያኛው ሚሌኒየም ማሞኛዎች ሲደጋገሙ መጀመሪያ “ኸረ ይሄ ነገር አያያዙ አላማረንም፣” አላልንም… በኋላ ነገሩ ያላማራቸው ጋዜጠኞች አነፍንፈው ደረሱበት እንጂ!

አሁንም የእሱን ችቦ ያነሱ ላለመኖራቸው ምን ማረጋገጫ አለን ! በሺዎች የሚቆጠር ሰው በሀሰተኛ ማስረጃ ሥራ በያዘበትና እድገት ባገኘበት ሁኔታ ባልሆኑት ነገር ሆንንብለው፣ የእነሱ ባልሆኑ ዙፋኖች ተኮፍሰው የሚያሰጨበጭቡን ላለመኖራቸው ምንስ ማረጋገጫ ይኖረናል!

እግረ መንገድ… ሰውየው ተመጽወቱኝ እያለ እየለመነ ነው፡፡ የአንድ ምግበ ቤት ባለቤትም… “ይሄኔ ትንሽ እንጨት ብትፈልጥ ኖሮ ለምግብ ገንዘብ ታገኝ ነበር፣” ይለዋል፡፡ የእኔ ቢጤው ምን ቢል ጥሩ ነው…

“መጀመሪያ የምግብ ዝርዝራችሁን ልየውና ከተስማማኝ እፈልጣለሁ፡፡”

ደግነቱ የትምህርት ማስረጃህን አምጣ አይባልም፡፡ ቢባልስ ምን ችግር አለው ! አንዱን ወዳጅ “ስማ፣ ፎርጅድ ዲግሪ የሚሠራልኝ ታማኝ ሰው ታውቃለህ?” ማለት ነው፡፡ ነገሮች ይህን ያህል የቀለሉ ይመስላል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here