የፍቃዱ ተ/ማርያም ኮሚቴ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠራ !

* የፍቃዱ አሟሟት አወዛጋቢ ሆኗል ፡፡

* የተሰበሰበው ብር መጠን አይታወቅም ፡፡

* ኮሚቴውና ቴዎድሮስ ተሾመ በገቢው ለይ አለመግባባት ፈጥረዋል ፡፡

* በቤተሰቦቹ መሀል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ፍ/ቤት ደርሷል ፡፡

ለአንጋፋው ተዋናይ ፍቃዱ ተ/ማርያም በተሰበሰበው የህክምና እርዳታ ገቢና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አርብ ጥቅምት 23 / 2011 ከጧቱ 3 :00 ሠዓት ካዛንቺስ በሚገኘው አፍሮዳይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠርቷል ፡፡

የአርቲስቱ እርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በጠራው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እስካሁን በመላው ዓለም ካሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሰባሰበው ገቢ በኮሚቴው የጋራ ሂሳብ መዝገብና

ከ” ጎ ፈንድ ሚ ” ተሰብስቦና ከሌሎች ምንጮች ተሰብስቦ በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ የግል ሂሳብ ቁጥር የተቀመጠው ጠቅላላ ገቢ ለሕዝብ በይፋ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

ፍቃዱ ተ/ማርያም ሁለት ኩላሊቶቹ ስራቸውን ማቆማቸው ለህዝብ በተገለጸ በቀናት ውስጥ የሚፈለገው ብር ቢሰበሰብም አርቲስቱን ወደ ህክምና ማድረስ ባለመቻሉ ሕይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል ፡፡

ፍቃዱ የህክምና ምርመራውን በሐገር ውስጥና በህንድ ሐገር ያደረገ ቢሆንም በመጨረሻ በዋቢ ሸበሌ ክፍተኛ ክሊኒክ የጀመረውን ህክምና አቋርጦ ወደ ጸበል እንዲሄድ ተደርጓል ፡፡

በወቅቱ ህክምናውን ሲከታተሉ የነበሩት የዋቢ ሸበሌ ዶ/ር ህክምናውን ማቋረጡ ለጤንነቱ አስጊ መሆኑ ቢነገረውም ፍቃዱ በቤተሰብ ግፊት ህክምናውን በፈቃዱ ማቋረጡን በፊርማው አረጋግጦ ወደ ጸበል ሄዷል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት ጸበል እየተጠመቁ በሀኪም የታዘዘን መድሀኒት የሚፈቀድ ሲሆን ፍቃዱ ግን እንደ እርሱ የስኳር ህመም መድሀኒት የሚወስድ ወንድሙ እና ፋርማሲስቷ ባለቤቱ ባሉበት ለአመታት የወሰደው የስኳር በሽታ መድሀኒቱን እንዲያቋርጥ ተደርጓል ፡፡

በዚህ የተነሳ ህመሙ እየተባባሰ ፣ ሰውነቱ እያበጠና ለሕይወቱ አስጊ እየሆነበት ቢመጣም ወደ ህክምና ሳይመለስ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል ፡፡

በተለይ በዚህ የሰለጠነ ዘመን ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት የማትከለክለውን የስኳር መድሀኒቱን እንዲያቋርጥ መደረጉ አነጋጋሪና ቤተሰቦቹን ለሁለት ጎራ የከፈለ አለመግባባት መፍጠሩ ከውስጥ አዋቂዎች ያገኘነው መረጃ ይገልጻል ፡፡

እንደ መረጃዎቻችን ገለጻ ለአርቲስት ፍቃዱ የተሰበሰበው ገቢ ቀድሞውንም ጥሩ የማይባለውን የቤተሰቦቹን አለመግባባት አባብሶታል ፡፡

በኮሚቴው ስም የተቀመጠው ወደ 1.1 ሚሊዮን ገደማ ብርና በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ እጅ የሚገኘው 73 ,000:00 ዶላር ወደ አንድ ቋት ይግባ የሚለው ሀሳብም ሌሎቹን የኮሚቴውን አባላትና ቴዎድሮስ ተሾመን አላግባባቸውም ፡፡

ይህ አለመግባባት ፣ በሁለቱም የባንክ ሂሳብ የተቀመጠው ገቢ በተናጠልና በድምር ምን ያህል እንደሆነ ፣ ከሕዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ ቀጣይ እጣፈንታና ከጋዜጠኞች ለሚነሱ ጥያቄዎች የኮሚቴው አባላት መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

ዳጉ ቲዩብ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here