የፖሊስን ጭካኔ በመቃወም በአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር የሚንበረከኩ ተጫዋቾች ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተባለ

የአሜሪካ የብሔራዊ እግርኳስ ሊግ አባላት የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት ከተንበረከኩ በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገለፀ።

ሊጉ እንዳሳወቀው ሰንደቅ ዓላማው ከፍ በሚልበት ወቅት መቆም የማይፈልጉ እስኪያልቅ ድረስ መልበሻ ክፍል መቆየት ይችላሉ።

ሊጉ ለሰንደቅ ዓላማውና ለብሔራዊ መዝሙሩ ክብር የሌላቸው የቡድኑ አባላት ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም አስታውቋል።

ተጫዋቾቹ በበኩላቸው መንበርከካቸው አሜሪካ ውስጥ ባሉ ጥቁር ህዘቦች ላይ በፖሊስ የሚደርሰውን ጭካኔ ለመቃወም እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልፀዋል።

የቡደኑ ኮሚሽነር ሮጀር ጉዴል በመግለጫቸው እንዳተቱት “በሜዳ ላይ የሚደረጉት እነዚህ ተቃውሞዎች የቡድኑ አባላት አገራቸውን እንማይወዱ የማስመሰል ትርጉም እየተሰጠው ነው” ይላሉ።

ጨምረውም “አባላቱ ለሰንደቅ ዓላማውም ሆነ ለሕዝባዊ መዝሙሩ ክብር ሊሰጡ ይገባል” ብለዋል።

 

በቀደመው በሊጉ ፖሊሲ መሰረት ተጫዋቾቹ ለብሔራዊ መዝሙሩ ሜዳ ላይ መገኘት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም መቆም አይገደዱም ነበር።

ክለቦቹ ተጫዋቾቻቸውን መቅጣት እንደሚችሉ አዲሱ ፖሊሲ ቢያስቀምጥም የክለቦቹን ቅጣት በተመለከተ ግን ዝርዝር አልተቀመጠም።

ይህ መግለጫም የብሐራዊ እግር ኳስ ሊግ ቡድን አባላት ማሕበራዊ ፍትህ ላይ ለሚሰሩ ጅማሮዎች 67 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ከገቡ በኋላ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here