ጋሽ ስብሐት ትግሬ ነው፡፡ በአድዋ አውራጃ ርባገርድ ነው የተወለደው፡፡ አንድም ቀን ስለ አንድ ዘር የበላይነት ሲያወራ ሰምተነው አናቅም፡፡

ስላገር እንኳ ጥቂት ነው የነገረን፡፡ እሱም በጣም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው፡፡ የሚያስጨንቀው ሰው ስለሚኖረው የመንፈስ ከፍታ ይመስለኛል፡፡

አገርን ሕብን የሚያጠፋ ሐሳብ ሲመጣ ግን ተነስቶ ሊጮኽ ይችላል፡፡ “ተስፋዬ ገብረ አብ እውነትና ውሽት በኬሚስትሪ ቀምሞ ተኩሶባችኋል፡፡

እኛ ሁላችን ሕዝብ በመሆናችን ለሕዝብ የተባለውን missile መከላኪያ ጋሻ ለናንተ ለመጠቆም የሰላም ምቾትና የአገር ፍቅር ያስገድደናል” ይላል፡፡

አንድ ጊዜ ከዘነበ ወላ ጋር ሲጫወት “ተመልከት እኔ በዘር ትግሬ ነኝ፡፡ አንተ ደግሞ ጋሞ ነህ፡፡ ማነው የሚያገናኘን? አማርኛ፡፡ ዕድሜ ለማን እንበል? ለምኒልክና ለጦረኞቹ፡፡

ፈረንሳይ ምን ይላል? ኦምሌት (የዕንቁላል ቂጣ) ለመሥራት ዕንቁላሎቹን መስበር ግድ ነው፡፡ ኤምፓዬር ለመገንባት ደግሞ በዘመኑ ያለውን ሙሉ አገር ነኝ የሚል የነገዶችና የጎሳዎች ዕንቁላል መስበር ግድ ነው፡፡ ሚኒልክም አደረገው፡፡ ምክንያቱም ዘመኑ አዘዘ፡፡

ጋሽ ጸጋዬ ኦሮሞ ነው፡፡ አባቱ ሮቤላ ይባላል፡፡ በምኒልክ ቤተመንግሥት ግብር አዳራሽ አጋፋሪ ነበሩ፡ ጓደኞቻቸው ስማቸውን በትክክል መጥራት ስለሚቸግራቸው ወሮ በሌ እያሉ ያሾፉባቸው ነበር፡፡ በኋላ ስማቸውን በክርስትና ስማቸው ቀየሩና ባንድ ቀን አዳር ገብረመድህን ተባሉ፡፡

ጸጋዬ የዚህ ዘር ጉዳዬ አገሩን አልሸፈነበትም፡፡ እንደውም እሱም እንደሚነግረን አባቱ ነበሩ ስለ አቡነ ጴጥሮስ የረኝነት ዕድሜና የጀግንነት ጀብድ በከፍተኛ አድናቆት ያጫወቱት፡፡

አንዳንድ የቅርብ ወዳጆቹ እንደሚነግሩን ከሆነ ደግሞ ጋሽ ጸጋዬ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም በትክክል ካልተጠራ ይናደድ ነበር፡፡

ሰቆቃው ጴጥሮስ ላይ እንዲህ ይለናል፡፡ “እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ÷ ተፈትቶ እንዳይከዳት ፈራሁ” ለሱ ኢትዮጵያ አጥንቱን ከአፈሯ ላይ የቀፈፈባት፣ ደሙን ከደሟ ላይ ያጠነፈፈባት፣ ወዙን ከወዟ ላይ የቀፈፈባት፣ በሕፃን እግሩ በህልም አክናፍ የከነፈባት ናት፡፡

ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ ያበባ እንቡጥ ሲፈነዳ

የግጦሽ ሣር ሲለመልም ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ

አዝመራው ጣል ከንበል ሲል ከብቱ ለሆራ ሲነዳ

ፈረስ ግልቢያው ሲሸመጥጥ ከወፎች ዜማ ስቀዳ

ልቤ በንፋስ ተንሳፎ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ

ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት

እመብርሃን ረሳሻት?
*
ተውኔቱንም የተመለከትን እንደሆነ በእናታለም ጠኑ ነጋ በሚባል ገጸባሕሪው እንዲህ ይናገረናል፡፡

ሰዎች ሕልማችሁ ምንድን ነው?

ፍቅር በእልህ ላይገታ

ሕልም በቂም ላይፈታ

ስሜት ኖሮን ስሜት ማገድ

ፈቃድ ኖሮን ፈቃድ ማገድ

እያለ ይወርድና

ሕዝቦች በጎ ሕልም አልሙ

ከትውልድ ወደ ትውልድ ዘላለም ከምናይ እኩይ

በማለት ፍቅርን እንድንመለከት ይጋብዘናል፡፡
***
ሀዲስ አለማየሁ አማራ ናቸው፡፡ ስለአንድ ዘር የበላይነት ሳይሆን አገራቸው ላይ ስለነበረ የተጓደለ አሠራር ነው የነገሩን፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲሀ ሲሉ እንሰማቸዋለን፡፡

ኢትዮጵያ እንደሌሎች አገሮች ሁሉ በጎም ክፉም ልማዶች ነበሩዋት፡፡ ዛሬም የቀሩት ቀርተው ያሉት አሉ፡፡

የቆዬ ልማድ የቆዬ በመሆኑ ሁሉ አይወድቅም፡፡ ወይም ሁሉ አይያዝም፡፡ መልካሙና ጠቃሚው ይያዛል፡፡ የሚሻሻለው ይሻሻላል፡፡ ሊሻሻል የማይችለው ይወድቃል፡፡

ነገር ግን የሚወድቀውም ክፉ ልማድ ከሥራ ይወገዳ እንጂ ከታሪክ ጸሐፊዎች መጽሐፍ ከደራሲዎች ድርሰት ሊወገድ አይገባም፡፡

ያለዚያ በየጊዜው የሚደረገው የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚክ ወይን ያስተዳደር የማኅበራዊ ኑሮ መሻሻል ከምን ተነስቶ እምን እንደደረሰ ሊታወቅ አይችልም፡፡
***
በዓሉ ግርማ ጅምናሳዳ ከተባለ ሕንዳዊ የተወለደ የኢሉአባቡራ (ሱጴ ቦሮ) ልጅ ነው፡፡

ኦሮማይ በሚለው መጽሐፉ ለዚች አገር ሕይወቱን አሳልፎ እስከመስጠት ደርሷል፡፡ ያሳዬን እውነትን ተናግሮ ስለሞመት እንጂ ስለ ዘር ትምህርት አልነገረንም፡፡

ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር

ያለ ሰው ቢወዱት ምን ያረጋል አገር
በማለት አገር ማለት ሰው ነው የለናል፡፡
**
እንዲፈቱ የምንፈልጋቸው አሁን ተፈተውልናል፡፡ ስለ ሁሉም ነገር ደስ ብሎናል፡፡ እናመሰግናለን፡፡

የተሻለ መንግሥት ወይም አስተዳደር እንዲመጣ ስንፈልግ ብዙ ደክመናል፡፡ ወይም ጊዜው ደርሷል ወይም ትንሽ ትዕግስት ያሰፈልጋል ይሆናል፡፡

እንደ ሕዝብ አንድ የምንሆንበት ጊዜ እንደሆነ ግን ማወቅ አለብን፡፡ እንደ ሕዝብ እራሳችንን ማሳየት ይኖርብናል፡፡ አሁን ጥሩ መሆን ተራው የኛ ሆኖአል፡፡

ኦቦ በቀለ ገርባ ምን አለ?

በፍቅር በልጠችሁ ተገኙ

በልማት በልጣችሁ ተገኙ

በመልካም ባሕሪ ልቃችሁ ተገኙ

በመደማመጥ ልቃችሁ ተገኙ

ሰውን በመጥላት ሳይሆን ሰውን በመውደድ በልጣችሁ ተገኙ፡፡

እሰክንድርም የደገመው ይህንኑ ነው፡፡ “ስልቱን አበላሽተን ግቡን ማሳመር አንችልም” ስልቱ ብጥብጥ ሊሆን አይችልም፡፡ ቅኝቱ ጭፍን ጥላቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ከጎጥ አሳብ ከፍ ማለት አለብን፡፡

አንድ ከመሆን የበለጠ ስልት የለንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል ” . . . . ዋኖቻችሁን አስቡ . . .” ብቸኛው መድኃኒት ፍቅር እንደሆነ እናስብ፡፡

መተሳሰብ ብቻ፡፡ መቀራረብ ብቻ፡፡ መሳሳብ ብቻ፡፡ ያነበብነው፣ ከዋኖቻችንም የሰማነው ይህንን ነው፡፡

ሰላም!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here