ዳሸን ባንክ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መርጃ የሚሆን 5 ሚሊዮን ብር ለብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለገሰ።

ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም በኮሚሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተከናወነው የልገሳ ስነ-ስርዓት ላይ የዳሸን ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት፣

በሕብረተሰቡ ውስጥ እንደሚገኝ ተቋም ዳሸን ባንክ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ የተነሳ በወገን ላይ የሚደርሰው ጉዳት በጥልቅ ይሰማዋል።

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ባንኩ ከመንግሰትና ሌሎች ባለድርሻ አካለት ጎን በመቆም የበኩሉን ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።

ከዚህ ቀደም ዳሸን ባንክ እምቦጭን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲሁም ለሦስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር መለገሱን አቶ አስፋው አስታውሰዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው፣

ዳሸን ባንክ ያሳየውን ቀና ተነሳሽነት አድንቀው ሌሎች ተቋማትም የባንኩን አርአያነት ተከትለው ከመንግሰት ጎን በመቆም ችግሩን ለመቅረፍ በጋራ መስራት አለባቸው ብለዋል።

የተለገሰው ገንዘብ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ምክትል ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የባንኩ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ተገኝተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here