ጎል ባልተቆጠረባቸው የመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ ጭካኔ በተሞላበት አጨዋወት 17 ፋውል ተመዘገበ። ጨዋታው ሲያበቃ ግን ብራዚል 3―1 አሸነፈች።

የፖላንድ እንዲህ መሸነፍ አርጀንቲና አራት ቡድኖችን ከያዘው ምድብ በአንደኛነት ለማለፍ ፔሩን ቢያንስ በሶስት ጎል ልዩነት የማሸነፍ ግዴታ ላይ ጣላት። ይህ ከሆነ ብራዚል በምድቡ በሁለተኛነት በማጠናቀቅ ከፍፃሜው ትቀራለች።

በዚያ ውድድር በሁለተኛ ዙርም የምድብ ጨዋታዎች ይደረጉና የየምድቡ አሸናፊዎች በቀጥታ ለዋንጫ ሽሚያ ይደርሱ ነበር።

የምነግራችሁ ስለ 1978ቱ የዓለም ዋንጫ ነው።

አርጀንቲና በወታደራዊ አምባገነን መንግስት ቁም ስቅሏን በምታይበት በዚያ ዘመን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን አዘጋጀች። ቡድኑ ዋንጫውን አሸንፎ የድሉ ፈንጠዚያ ለሃገር ውስጡ የፖለቲካ ትርምስ ሽፋን እንዲሆን ተፈልጓል።

ለዓላማው መሳካት ደግሞ በቅድሚያ አርጀንቲና ፔሩን ቢያንስ 3―0 መርታትና ከምድቡ በአንደኛነት ማለፍ ግዴታዋ ሆነ።

ግን የሶስት ጎል ልዩነት ድል እንደ ጭራቅ ለሚታዩት ለአርጀንቲናው ጁንታ መሪ ጄኔራል ሆርጌ ራፋኤል ቪዴላ ርቆ የተሰቀለ ተስፋ ሆነ።

ስለአርጀንቲና እና ፔሩ ግጥሚያ ሲያስቡ ብራዚላዊያን ጥርጣሬ ገባቸው። የፔሩ ግብ ጠባቂ ራሞን ኪሮጋ በትውልድ አርጀንቲናዊ በመሆኑ የሴራ ንድፈ ሃሳብ እንቅልፍ ነሳቸው።

ከዓመታት በኋላ (ማስረጃ ባይኖራቸውም) የተለያዩ ምስክሮች ለአውሮፓ ጋዜጦች እነዚህን መረጃዎች አቀበሉ።

ከወሳኙ የምድብ ጨዋታ በፊት የአርጀንቲና መንግስት 35ሺህ ቶን ስንዴ እና የጦር መሳሪያ ወደ ፔሩ ላከ። የአርጀንቲና ማዕከላዊ ባንክ እንዳይንቀሳቀስ አግዶት የሰነበተውን 50 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የፔሩን ቋሚ ንብረት ለቀቀላት።

በ70ዎቹ በላቲን አሜሪካ አምባገነን ገዢዎች መካከል የተፈረመ የአንዳቸውን የፖለቲካ ተቃዋሚ ሌላኛቸው በወዳጅነት የማይመለከቱበት “Condor Plan” የተባለ ስምምነት ነበር። ጨዋታው የስምምነቱ መፈፀሚያ አንድ አካል ተደረገ።

የፔሩ ወታደራዊ መሪ ፍራንቼስኮ ሞራሌስ ቤርሙዴዝ 13 የፖለቲከኛ እስረኞቻቸውን የአርጀንቲና መንግስት እንዲያሰቃይላቸው ወደ ቡዌኖስ አይረስ ላኩዋቸው። የአርጀንቲና መንግስትም እስረኞቹን ለማሰቃየት ሲቀበል ፔሩ በአፀፋው ፍላጎቱን እንድትፈፅምለት ቃል በማስገባት ነበር።

ጨዋታው በብዙ ጎል ልዩነት ፣ በአርጀንቲና አሸናፊነት መጠናቀቅ አለበት። እንዴትም ትፈጽመው፣ ፔሩ ስምምነቱን መፈፀም ነበረባት።

ጨዋታው ተደረገ።

ውጤት?…አርጀንቲና 6 – ፔሩ 0……

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here