ቤርናዴት ማልዳ ትነሳለች። አንድ ሰዓት እንኳን ሳይሞላ ቀኗ ይጀመራል። ቁርሷን ትበላለች፣ ባለቤቷን ለመንከባከብ ራሷን ታዘጋጃለች። ልብስ ትቀይርለታለች። ምግብ ታበስልለታለች።

ወደ መፀዳጃ ቤት ትወስደዋለች። ቆሻሻውን ሁሉ ታፀዳለታለች። ጡንቻውን ታፍታታለታለች። ይህ የአንድ ቀን ብቻ ልማዷ አይደለም። ላለፉት 35 ዓመታት አድርጋዋለች። በየዕለቱ ደጋግማዋለች። እስከ መጨረሻው ላታቋርጥ ለራሷ ቃል ገብታለች…

ፈረንሳይ በጄኔራል ሻርል ደጎል አመራር ስር ሳለች፣ የመንግስት ወግ አጥባቂ አስተዳደር እያደር የህዝብ ቅሬታ ሲያስነሳ ዘመኑ በ1960ዎቹ ነበር። ጥቁሮች ከነጭ ፈረንሳዊያን ጋር በጋብቻ ከተጣመሩ ጉድ የሚባልበት ያ የዘረኝነት ዘመን…።

ጥቁሩ ዣን ፒዬር አዳምስ ግን ከነጯ ቤርናዴት ጋር በፍቅር ወደቀ። ወደደችው፣ ወደዳት። ሃገር ጉድ ይበል ብለው ፍቅራቸውን እስከ ጋብቻ አደረሱት። ገና አማተር ተጫዋች ሳለ ነበር የተዋወቁት። በ1969 ከጋብቻ በኋላ፣ ከፍተኛ ዲቪዚዮን የነበረው ኒም ፕሮፌሽናል ኮንትራት አቀረበለት። ተቀበለው።

ዣን-ፒየር እና ቤርናዴት ኑሯቸውን ወደ ኒም ከተማ አዛወሩ። በፍቅር ሲኖሩም ወንድ ልጅ ወለዱ። 1970ዎቹ ለጥንዶቹ አስደሳች ዘመናት ነበሩ። አዳምስ ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጥቁር ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።

ዝና፣ ገንዘብ፣ መሽቀርቀር፣ መደሰት የአዳምስ የዕለት ተዕለት ልማድ ነበር። ቀልድ ያውቃል። ፈገግታ ከፊቱ አይጠፋም። ዝና ሲጨመርበት ደግሞ… አለ አይደል… አብሮ የሚስቅም አይጠፋም።

ገና የ10 ዓመት ብላቴና ሳለ አያቱ በመንፈሳዊ ጉዞ ሰበብ ይዘውት ከመጡ በኋላ የሴኔጋሉ ልጅ ፈረንሳይን ቤቴ ብሏል። ፓሪ ሰን ዠርመ እና ኒስን ጨምሮ እስከ 1981 ድረስ በዲቪዚዮኑ ለእውቅ ክለቦች ተጫወተ።

34 ዓመቱ ላይ ጫማውን ሰቅሎ፣ ለቀሪው ህይወቱ ህፃናትን ለማሰልጠን ለትምህርትና ልምምድ ወደ ዲዦ ከተማ አቀና። እዚያም በልምምድ ላይ ሳለ በጉልበቱ ላይ ጉዳት ደረሰበት።

የሊጋሜንቱን ህመም ለመገላገል በሊዮን ከተማ በሚገኘው ኤድዋርድ ሄሪዮ ሆስፒታል ምርመራ አደረገ። ጉዳቱ ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልገው በማረጋገጡ ለኦፕሬሽኑ ቀን ተቀጠረ። የቀን ጎዶሎ፣ ማርች 17 ቀን 1982…።

አዳምስ ቀጠሮውን ጠብቆ ቢመጣም በሃገሪቱ የጤና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል። ህሙማን ብዙ ቢሆኑም ሃኪሞች ጥቂት ነበሩ። የአዳምስ ቀዶ ጥገና አስቸኳይ ባለመሆኑ እንደገና ሊቀጠር ይችል ነበር። ሆኖም ባሉት ባለሙያዎች ጉልበቱ ሊከፈትና ሊጠገን ተወሰነ።

አንድ የማደንዘዣ ባለሙያ ብቻ ስራ ላይ ነበረች። ተለማማጅ ተማሪዎችም አሉ። ህሙማን እንደ ቦኖ ውሃ በየተራ ማደንዘዣ ተሰጣቸው። አዳምስ ተራው ደርሶ አሸለበ። ግን እንደተጠበቀው አልሆነም።

ጉልበት ላድን ያለው ህክምና እጅና እግሩን ጨምሮ መላው አካላቱን ከጥቅም ውጭ አደረጋቸው። ከአይኖቹ ሽፋሽፍት በስተቀር ቢጠሩት እንኳን ፊቱን ዞር ማድረግ ተሳነው። አንደበቱ ተዘጋ፣ በድጋሚ መናገር አልቻለም።

የማደንዘዣው ሂደት የህክምና ስህተት ነበረው። ተለማማጆቹ ወደ ሰውነቱ ያስገቧቸው ትቦዎች እንኳን በቅጡ አልተሰኩም። ወደ ሳንባው የተላከው ትቦ የአሰካክ ስህተት ስለነበረው ሳምባዎቹ በቂ ኦክስጅን ባለማግኘታቸው የልቡ ስራ ተስተጓጎለ። አንጎሉ በቂ ኦክስጂን ባለማግኘቱ ለአደጋ ተጋለጠ።

ያ ፈርጣማ ተከላካይ ሰውነቱ ከዳው። መላወስ አቃተው። በዚያች እርጉም ቀን ያለ ድጋፍ ወደ ሆስፒታል ቢገባም፣ በራሱ አቅም ወደ ቤቱ መመለስ አልቻለም።

ቤርናዴት ለአምስት ቀን በሆስፒታል እየዋለች፣ እያደረች ጠበቀችው። ፍቅሯ፣ የልጇ አባት፣ የህይወቷ ጓድ ከተኛበት ሳይነሳ ቀረ። ከእንግዲህ በሰው ድጋፍ እንጂ በራሱ አቅም መንቀሳቀስ እንደማይችል ቁርጡን ነገሯት። የህክምና ኃላፊዎች ለአረጋዊያን መንከባከቢያ ማዕከል እንድትሰጠው መከሯት።

ለቤርናዴት ይህ የሰነፎች ምክር ነበር። አልተቀበለቻቸውም። “ወደ ቤታችን እወስደዋለሁ፣ እዚያም እስከመጨረሻው እንከባከበዋለሁ” ብላ ወሰነች። በደግ ዘመን ፍቅርን ወዳዩበት ቤታቸው አመጣችው።

2018…፣ ዣን ፒየር አሁንም በህይወት አለ። ዕድሜው 69 ደርሷል። ቤርናዴትም አልሰለቸችም። ዕድሜ ተጭኗት ቆዳዋ ተሽብሽቧል። የዚያ ዘመን ውበቷ ረግፏል። እርጅና ቤት እየሰራባት ነው።

ግን እጅ አልሰጠችም። ባሏን መንከባከብ የዕለት ተዕለት ስራዋ ከሆነ 36ኛ ዓመቷን ልትደፍን አንድ ወር ገደማ ቀርቷታል። ዘመናት ቢያልፉም ታማኟ ሴት ግን ሰው ሰራሽ ስህተት አልጋ ላይ የጣለውን ሸበላ አይኗ እያየ ልትጥለው አልፈቀደችም።

የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ክለቡ ከሚገኝበት ኒም ከተማ አቅራቢያ ዣን ፒየር አዳምስ አሁንም ተኝቷል። ዛሬም ቤርናዴት ከጎኑ አለች። ከአደጋው በኋላ በእያንዳንዷ ቀን እንዳደረገችው ሁሉ ዛሬም ማልዳ ትነሳለች። ታጥበዋለች፣ ታለብሰዋለች፣ ትመግበዋለች፣ ከመተኛት ብዛት ጎኑ እንዳይላላጥ ታገላብጠዋለች። አልታከተችም፣ አልሰለቸችም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here