በአንድ ወቅት መልካቸው ነጭ፣ ጥቁር እና ግንባረ-ቦቃ የሆኑ ሶሥት በሬዎች ጫካ ውስጥ ይኖሩ ነበር።
አንበሳን ጨምሮ የትኛውም አውሬ ቢመጣ ክብ በመስራት እየተዋጉ አላስጠጋ ይላሉ።
አንድ ቀን ግን አያ ጅቦ መጣና “ይሄ ነጭ በሬ ያስጨርሳችኋል፤ እሱ ባይኖር እኮ በጨለማ አትታዩም” የሚል መጥፎ ሀሳብ በውስጣቸው ለቀቀባቸው።
እናም ሁለቱ በሬዎች ስጋት ስላደረባቸው ተባብረው #ነጩን_በሬ አባረሩት፡፡
ጅቡም ነጩን በሬ ብቻውን ስላገኘው በላው።

ጅቡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተመለሰና ለጥቁሩ በሬ እንዲህ ሲል ያማክረዋል፤
ግንባረ ቦቃው ካለ አሁንም ለአደጋ የተጋለጥህ ነህ” ምክንያቱም ግንባሩ ላይ ነጭ ስላለሁ በቀላሉ ያስጠቃሃል አለው፡፡
በዚህም የተነሳ ሁለቱ በሬዎች ተለያዩ፡፡ በዚህ ሰአት ጅቡ #ግንባረ_ቦቃ በሬ ለብቻው ተነጥሎ ስላገኘው በላው።

በሌላ ቀን ጅቡ #ጥቁር በሬው ጋር ይሄዳል፡፡

በሬውም “ዛሬ ደግሞ ምን ፈልገህ መጣህ? ልትበላኝ ነው?” ሲል ጠየቀው።
ጅቡም “አንተ እኮ የተበላኸው መጀመሪያ ጓደኛህን አሳልፈህ የሰጠህ ጊዜ ነው” ብሎ በመጨረሻ ጥቁሩን በሬ በላው፡፡ ይባላል…
ከሀዲስ አለማየሁ፡ ተረት ተረት- የመሠረት ከሚለው መፅሀፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here