የጉድ አገር እኮ ላይ ነን ያለነው ጎበዝ ።

የኢትዮጵያ እግር ኳሥ ፌዴሬሽን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋርን እያንዳንዳቸውን 150 ሺ ብር ቀጥቻቸዋለሁ ብሏል ።

ለነገሩ ከቅጣት ከ600 ሺ እስከ 1 ሚሊየን ብር ገቢ አስገባለሁ ብሎ እቅድ የያዘ ፌዴሬሽን በሰበብ አስባቡ ክለቦችን እየቀጣ ካዝናውን ማደለቡ ላያስደንቀን ይችላል ።

በጣም የገረመኝ ለጅማ አባጅፋር የሸለመውን (ሽልማት ከተባለ ) 150 ሺ ብር በቅጣት ሠበብ መልሶ በእጁ አስገብቶታል ።

ይህ በእውነት ያስቃል ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻውን በዚህ አመት በድምሩ 290 ሺ ብር የቅጣት ሠለባ ሆኗል ።

መቀለ ከተማ ፣ ወልድያ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ወልዋሎና ሌሎች ክለቦች ተቀጥተው ፌዴሬሽኑ ከ1.2 ሚሊየን ብር በላይ ከእቅድ በላይ ከቅጣት ገቢ አግኝቷል ።

ወደው አይስቁ !!

የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን ክለብ ሽልማት እና ቅጣት እኩል የሆነባት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች ።

ከ14 እስከ 18 ሚሊየን ብር ወጭ ለሚያወጣ ክለብ ሲጀመር 150 ሺ ብር ሽልማት ብሎ መስጠት ሲበዛ ያሳፍራል ።

ሂዱ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ ሻምፒዮን የሆነበትን እና Tv right ጨምሮ የተለያዩ ገቢዎችን አካቶ ዘንድሮ 149.4 ሚሊዮን ፓውንድ ማግኘት ችሏል ።

በርግጥ በገቢ ረገድ 149.7 ሚሊዮን ፓውንድ የሠበሰበው ማንችስተር ዩናይትድ ከፍተኛ ተከፋይ ነው ።

እነዚህ ክለቦች የሦስት አመት የተጫዋቾቻቸው ደሞዝ አያሳስባቸውም ።

ልብ በሉ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሁሉም ክለቦች ገቢዎች ተሠልተው ይከፈላቸዋል ።

ሀያኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ዌስትብሮሚች እንኳን 95 ሚሊዮን ፓውንድ አግኝቷል ።

ይህ ማለት ለዚህ ክለብ የሙሉ ተጫዋቾቹን አመታዊ ደሞዝ አንደላቆ የሚከፍል ነው ።

በነገራችን ላይ አርሠናል 142 ሚሊዮን ፓውንድ ፣ ቸልሲ 140 ፣ ሊቨርፑል 145 ፣ ቶተንሀም 143 ሚሊዮን ፓውንድ ባለቤት ሆነዋል ።

የኛ ሊግ 150 ሺ ብር ሽልማት አይደለም የተጫዋች ደሞዝ ይቅርና ለተጫዋቾች የአንድ ቀን ደህና እራት እንኳን አይጋብዝም ።

ለብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ 120 ሺ ብር የወር ደሞዝ የሚከፍል ፌዴሬሽን አመቱን በሙሉ ለፍቶ ላሸነፈ ክለብ 150 ሺ ብር ሸልሜያለሁ ይላል እሱንም በእጅ አዙር መልሶ ይቀበላል ።

ድንቄም ሽልማት !

በእንግሊዝ ክለቦች የቅጣት ሠለባ ከሆኑ ከፍተኛው 50 ሺ ፓውንድ ነው ።

የተለመደው ደግሞ ከ5 ሺ እስከ 15 ሺ ፓውንድ ነው ።

በ 50 ሺ ፓውንድ እና በ 149.4 ሚሊዮን ፓውንድ ያለውን ልዩነት እስኪ ተገንዘቡት ?

ፌዴሬሽኑ የቅጣት ውሳኔ እና የሽልማት አሠጣጥ ስርአቱን በደምብ ሊገመግም ይገባል ።

ቅጣት ላይ ማቻቻል የሚባል ነገር አይሠራም ። በእኛ ሊግ ግን እየሆነ ያለው ነገር ይህ ነው ።

ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ ቢታመንም የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ ለቀጣዩ የውድድር አመት በደምብ ተፈትሾ እና

ክለቦች ተወያይተውበት አንድ ማሠሪያ ካልተበጀለት የፌዴሬሽኑ ሥራ አሥፈፃሚዎች መሳሳታቸውን ፣

ክለቦችም አቤት ማለታቸውን ፣ እኛም መተቸታችንን አናቆምም ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here