ፍርድ ቤቱ በስራ ማቆም አድማ ተጠርጥረው የነበሩት የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሺን 9 ሰራተኞች በ20 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ፈቀደ።

መርማሪ ፓሊስ በኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን 9 ሰራቶች ላይ ባደረገው ምርመራ በህዳሴው ግድብና የባቡር ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ እጃቸው እንዳለበት አረጋግጫለሁ በማለት

ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የቀረበው ጥያቄ አሳማኝ አይደለም በማለት የፓሊስን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው በ20 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ፈቅዷል።

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ተረኛ የወንጀል ችሎት የተጠርጣሪዎችን ጠበቃ አስተያየትና የመርማሪ ፓሊስ የምርመራ ውጤት አድምጧል።

በዚህ ወቅት መርማሪ ፓሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ስምንት ቀን ጊዜ በርካታ የምርመራ ስራዎች መስራቱን የገለፀ ሲሆን፥ ተጠርጣሪዎቹ ከህዳሴው ግድብና የባቡር ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ማስረጃ ማግኘቱን አስታውቋል።

እንዲሁም ወንጀሉ ከስራ ማቆም የመብት ጥያቄ ጀርባ ሌላ አለማ እንዳለው የሚያመላክት በመሆኑ ሰፊ ምርመራ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፓሊስ ጠይቋል።

የዘጠኙ ተጠርጣሪዎች ጠበቃ በበኩሉ የተጠርጣሪዎች የመብት ጥያቄ ከስምንት ዓመት በፊት ጀምሮ የጠየቁትና እየተጠባበቁት የነበረ ሲሆን፥ ከመብት ጥያቄ ውጭ ሌላ አላማ የሌላቸው መሆኑንና

የባቡርና የህዳሴው ግድብ ሰራቶች የስራ ማቆም አድማ እንደማይመለከታቸው በመጠቆም ፓሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜና ምክንያት አግባብነት የሌለው በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም ጠበቆች የሙያ ስነ ምግባራቸውን በመጠበቅ ለተጠርጣሪ መቆም ብቻ ሳይሆን ወንጀልን በመከላከል ረገድ ፍርድ ቤቱን ሊያግዙ ይገባል ያለ ሲሆን፥ ፓሊስ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ አይደለም በማለት ተጠርጣሪዎቹ በ20 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ፈቅዷል።

ፓሊስ የይግባኝ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ፍርድ ቤቱ መግለፁን ተከትሎ ይግኝ መጠየቁ ተነግሯል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here