የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ስልጣናቸውን በሰላማዊ  መንገድ እንዲያስረክቡ ጠየቁ፡፡

ፕሬዝዳንት ካቢላ የመሪነት የስልጣን ቆይታቸው ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ለማድረግ በመንቀሳቀሳቸው ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ 2016 መጨረሻ ላይ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ባደረጉት ድርድር  ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተስምምነት ደርሰው እንደነበር አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል፡፡

ዋና ፀሃፊው ጥሪውን ያቀረቡት ፕሬዝዳንት ካቢላን ተቃውመው አደባባይ የወጡ ሰዎች ላይ የካቢላ ፀጥታ አካላት 7 ሰዎች መግደላቸውን እና 120 ሰዎች ማሰራቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ ከዓመት በፊት እርሳቸውን የሚተካ መሪ በምርጫ ወደ ስልጣን እንዲመጣ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁ ተናግረው ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ በቃላቸው አልተገኙም ተብሏል፡፡

በመሆኑም ዋና ፀሀፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ፕሬዝዳንቱ የገቡትን ቃል በማክበር ምርጫ እንዲያካሂዱ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስልጣን እንዲያስረክቡ ጥሪ አቅርበዋል።ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ወጥተው ማሰማት እንዲችሉ ሊገደቡ እንዳይገባም አስምረውበታል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች  በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያና ወከባ ከማድረስ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሬዝዳንት ካቢላ ስልጣን እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ፡ አልጀዚራ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here