ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአገሪቱን የመልማት መብት ከማስከበር ባለፈ ለቀጠናው አገሮች ጭምር የጎላ ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ
በተቻለ ፍጥነት ከግብ መድረስ እንዳለበት የውጭ ዜግነት ያላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ገለፁ።
በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የውጭ አገር ተማሪዎችና መምህራን ይህንን የገለፁት የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ግንዛቤ ለማሳደግ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።

 

የግድቡን ግንባታ በተመለከተ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን ጨምሮ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተካሄዱት ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች፣

በተፋሰሱ አገሮች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶቹን ለማስወገድ በመካሄድ ላይ የሚገኙት ምክክሮች የመድረኩ ዋነኛ ትኩረቶች ነበሩ።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ  እያካሄደች ያለው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጥረት፣ የሶስትዮሽ ምክክርና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀምን የተመለከቱ ፅሁፎች ቀርበዋል።

በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው፤ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቡን የምትገነባው አሁን ካለችበት የእድገት ደረጃና ቁጥሩ በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ብዛቷ አንጻር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

የህዳሴ ግድቡ የግንባታ ሂደትም ሆነ የመጨረሻ ግብ በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች አሉታዊ ተፅእኖ በማይፈጥርበት መንገድ የሚካሄድ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተብራርቷል።

ግድቡ ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊ ምሁራን አውስተዋል።

ከተፋሰሱ አባል አገሮች መካከል ከግድቡ ጋር በተያያዘ መግባባትንና መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል ተግባር በኢትዮጵያ በኩል እየተከናወነ መሆኑን ያመለከቱት ፅሁፍ አቅራቢዎቹ፤ ተመራማሪዎች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የግድቡን ግንባታ ሂደት በአካል እንዲጎበኙት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የሚደረገው የሶስትዮሽ ምክክር በጥሩ የመግባባት መንፈስ በመካሄድ ላይ መሆኑም ተገልጿል።

‘በአሁኑ ወቅት ግብፅ የግድቡን ግንባታ ከመቃወም ወጥታ የግድቡ የውሃ ሙሌትና አስተዳደር ሊኖረው በሚገባው ሂደት ላይ ወደ መደራደር መጥታለች’ ሲሉም ምሁራኑ አብራርተዋል።

ከተለያዩ የዓለም አገሮች የመጡና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችና መምህራን በበኩላቸው ግድቡ ከአገሪቱ ህዝብ አልፎ ለቀጠናው አገሮች ጠቀሜታ እንዳለው የሚገነዘቡ መሆኑን ገልፀዋል።

የደቡብ ሱዳን ዜጋ የሆነው አሙሌ ኒክሰን እና የርዋንዳው ንታኪሌሙንጉ ማትው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት አገራቸውን ጨምሮ በድህነት ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የሚተርፍ ስራ ነው።

‘በመሆኑም ስራውን ከማቀላጠፍ በተጨማሪ በተፋሰስ አገሮቹ መካከል በተለይ ከግብጽ ጋር አለ ተብሎ የሚነገረውን አለመግባባት መልክ ማስያዝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል’ ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ኬ ኤን ሲንግ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ቀድሞ መሰራት ካለበት የዘገየ ስራ መሆኑን ነው የገለፁት።

”ሃብታቸው ላይ መወሰን የሚችሉት እራሳቸው ሃብቱ የሚገኝባቸው አገሮች በመሆናቸው የውሃ ማማ የምትባለው ኢትዮጵያ እየተጠማች በቀኝ ገዢዎች የተቀመጠላቸውን መብት ለማስከበር መጣርም ተገቢ አይደልም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እየሰራች ያለው ስራ ተገቢ መሆኑንም ፕሮፌሰር ሲንግ አመላክተዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ  አቶ ሃይሉ አብርሃም በበኩላቸው ‘ኢትዮጽያ ግድቡን የምትገነባው የህዝቦቿን ኑሮ ለማሻሻል እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይደልም’ ብለዋል።

በመሆኑም የዓለም ህዝብ ከዚህ አንጻር ሊገነዘባት ይገባል በማለት የመድረኩ ተሳታፊዎችም በየሄዱበት አካባቢ  እውነታውን በማሳወቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here