የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 46 ከንዑስ አንቀጽ አንድ ጀምሮ ‹‹የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው፤

ክልሎች የሚዋቀሩትም በሕዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በማንነት እና በፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው›› ይላል፡፡

እነዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች በሀገር ውስጥ የሚነሱ ‹‹የወሰን ይገባኛል›› ውዝግቦችን ለመፍታት ምን ያህል ጥቅም ላይ ውለዋል?

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ቻላቸው ታረቀኝ ‹‹የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 46 ድንጋጌዎች በሚገባ ተሠርቶባቸዋል ለማለት አያስደፍርም›› ብለዋል፡፡

ለዚህ ሐሳባቸው ማጠናከሪያ ደግሞ ‹‹ፈቃድን ወይም የሕዝብ ይሁንታ ባለማሟላታቸው ነው›› የሚለውን አመንክዮ አስቀምጠዋል፡፡

‹‹የውጭው ዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየው ‹ከዚህ ክልል ነው መኖር ያለብኝ› ብሎ የሚወስነው ራሱ ሕዝቡ ነው›› ብለዋል አቶ ቻላቸው፡፡

የፖለቲካ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ኃላፊነታቸው የሕዝብን ፍላጎት ማስፈፀም መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ትክክለኛ ዴሞክራሲ በሚተገብሩ ሀገራት ውሳኔዎች የሕዝብ ይሁንታን ተከትለው እንደሚፈፀሙም ነው ምሁሩ ያስረዱት፡፡

‹‹የግዛት ወሰን ሥሪቱም በአንቀጽ 46 ከተጠቆሙት ነጥቦች መቅረት የሌሉባቸው ተጨማሪ መስፈርቶችን ማሟላት ይገባው ነበር፤

አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ አምስት መካተት ወይም ግንዛቤ ውስጥ መግባት ነበረበት›› በሚል ነው አቶ ቻላቸው የሚሞግቱት፡፡

የኢፌዴሪ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ አምስት ‹‹በዚህ ሕገ-መንግሥት ውስጥ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን ባሕርይ የሚያሳይ ማኀበረሰብ ነው፡፡

ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ፣ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣

ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣

የሥነ-ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው›› ሲል በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ሥነ-ልቦና ሲባል አለባበስ፣ አለቃቀስ፣ ፀጉር አሠራር እና ሌሎች የሚታዩ እና የማይታዩ እሴቶችን በውስጡ ያካተተ መሆኑንም ምሁሩ አብራርተዋልል፡፡

ስለዚህም ‹‹ሥነ-ልቦና በአንቀጽ 46 ላይ መካተት ነበረበት፤ ታሪክም እንደ አንድ መስፈርት መወሰድ አለበት›› ይላሉ፡፡

‹‹የወሰን አከላለሉ ክልል አንድ፣ ክልል ሁለት፣ ክልል ሦስት፣… ተብለው በተዋቀሩበት አመዳደብ ተመሰረተ እንጂ በሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 46 የተቀመጡትን ሐሳቦች መሠረት ተድረጎ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው›› ሲሉም ክፍተቱን ተችተዋል፡፡

የወሰን ጉዳዮች በኢትዮጵያ ሕዝብን ከሕዝብ ደም የሚያቃቅሩ፣ ውጥረትን የሚያነግሡ እና ሰላምን የሚያደፈርሱ ሰበቦች ከሆኑ መሰነባበታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከምሁራን ጋር በመምከር ፈጣን እልባት መስጠት እንደሚኖርባቸው አቶ ቻላቸው አሳስበዋል፡፡

(አብመድ)፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here