የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) መሃከሉ ላይ የአክሱም ሃውልት ያለበት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ ያውለበልባል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የተካሄውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ከሃገር ውጪ ነፍጥ አንግበው የኢትዮጵያን መንግሥት ሲወጉ የነበሩ ቡድኖች ወደ ሃገር እየተመለሱ ነው።

ከእነዚህም መካከል ትናንት 2000 የንቅናቄውን ሰራዊት ይዞ ዛላምበሳ የደረሰው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ይገኘበታል።

ድርጅቱ ባለፈው ነሀሴ ወር ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በአሥመራ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ወደ አገር ቤት ገብቶ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ መስማማቱን የሚታወስ ነው።

ለመሆኑ ትህዴን መቼ ተመሰረተ ?

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) በ1993 ዓ.ም በአሥመራ ተመስርቶ ላለፉት 17 ዓመታት በኤርትራ መንግሥት ወታደራዊና የትጥቅ ድጋፍ ሲደረግለት እንደቆየ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራና ሶማልያ አጣሪ ቡድን የተጠናቀረ ሪፖርት ያሳያል።

የኤርትራ መንግሥት በተለይ የድርጅቱ ደንብ ቁጥር 1907 (2009) በመጣስ ለታጣቂ ኃይሉ ድጋፍ ያደርጋል የሚል ክስም አቅርቦ ነበር።

በትግራይና በኤርትራ ድንበር አከባቢ የሚንቀሳቀሰው ትህዴን፤ በአከባቢው ደምሒት የሚል መጠሪያው ስሙ ይበልጥ ይታወቃል።

ቡድኑ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) 1993 ዓ.ም ላይ ባለመግባባት የተነጠሉ የቀድሞ ታጋዮች የመሰረቱት ሲሆን፤ ከመስራቾቹ አንዱ የሆነውና የድርጅቱ ከፍተኛ መሪ የነበረው አቶ ፍሰሃ ሃይለማርያም በ1997 ዓ.ም ላይ ተገድሎ ተገኝቷል። ገዳዮቹም ሆነ አሟሟቱን የሚመለከት ምንም አይነት ይፋዊ መረጃ የለም።

ትህዴን ሊታገልለት የተነሳው ዓላማ ምን ነበር?

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) መሃከሉ ላይ የአክሱም ሃውልት ያለበት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ አለው።

ትህዴን በድረ-ገፁ እንዳሰፈረው የሚታገልለት ዓላማ፤ በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች መብት ሙሉ ለሙሉ የሚከበርበት ዴሞክራሲያዊ መንግሥትና ስርዓት ለመመስረት ነው ይላል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራና ሶማልያ አጣሪ ቡድን አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት፤ ትህዴን በምስራቃዊ የኤርትራ ክፍል ሓሬና በተባለው ደሴትና በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ሌላ አነስተኛ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንደነበረው ቡድኑ ይገልፃል።

መርማሪ ቡድኑ የቀድሞ ጄነራሎችን ዋቢ በማድረግ፤ ቡድኑ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ነፍጥ ካነሱ ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል የነበረው ነው ይላል። እስከ 20 ሺህ ወታደሮች እንደበሩት በመጥቀስ።

“የኤርትራ መንግሥት ለሌሎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከሚያደርገው ድጋፍ ሁሉ ለዚህ ቡድን የሚሰጠው ድጋፍ የላቀና የተደራጀ ነበር” ይላል የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት።

አጣሪ ቡድኑ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አልፎ አልፎ ወደ ኢትዮጵያ በተለይ ወደ ትግራይ እየዘለቀ ከሚያደርሰው ወታደራዊ ጥቃት በተጨማሪ ሌላ ተልዕኮም ነበረው ይላል።

የድርጅቱ አባላት ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይበልጥ ታማኝ ስለነበሩ በአሥመራና በቤተ መንግሥት አከባቢ የፀጥታና ደህንንት ጉዳዮች ዙሪያ እስከማማከር ደርሰው እንደነበር የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ይጠቁማል።

ይህንን ውንጀላ የኤርትራ መንግሥት እንደማይቀበለው በወቅቱ የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ የማነ ገብረአብ ኣሳውቀው ነበር።

የትህዴን ጣልቃ ገብነት በኤርትራ ህዝብ ዘንድ ቅሬታ አስነስቶ እንደነበርም ይነገራል።

በቅርቡ ከኤርትራ በዛላምበሳ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የትግራይ ህዝብ ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ሊቀመንበር እና አባል ስለ የወደፊት እቅዳቸው ይህን ይላሉ ።

Posted by Gudu Kasa on Sunday, October 14, 2018

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here