1ኛ/ በመታወቂያው ቦታ ላይ ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ በ7 ቢሮዎች ማውጣት እንደሚጀመር መግለጻችን ይታወሳል። ሆኖም እስካሁን ባለመጀመሩ የሚመለከተውን ባለስልጣን አነጋግረናል። በዚሁ መሰረት እስካሁን መጀመር ያልተቻለው ለዝግጅት ጊዜ በማስፈለጉ ነው። ባለስልጣኑ ባሳወቁን መሠረት ከመጪው ማክሰኞ ጀምሮ በ8 ቦታዎች ላይ መታወቂያውን ማውጣት ይጀመራል።

2ኛ/ ጊዜ ገደቡም እንዲጨመር ጥያቄ አቅርበናል። በዚሁ መሠረት በ2ኛው ወር እስከ 15ኛው ቀን የነበረው እስከ ወሩ መጨረሻ እንደሚያቆዩ ቃል ገብተውልናል።

3ኛ/ ከ3ኛው ወር ከቀን 1 (March 1/2018) ጀምሮ ማንኛውም አዲሱን መታወቂያ ያልያዘ ለቅጣት እንደሚዳረግ ገልጸውልናል።

4ኛ/ አገሬ ቢገባ ይሻለኛል የሚትሉ ከወዲሁ እንቅስቃሴ እንድትጀምሩ እናሳስባለን።

5ኛ/ አገር ለመግባት ምንም ሰነድ የሌላችሁ ወደ ኤምባሲያችን በመምጣት ለቆንስላ ክፍል ማመልከት የምትችሉ መሆኑን እንጠቁማለን።

6ኛ/ የልማት ማህበራት፣ የኮሚኒቲ፣ ሌሎች የኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶች አባል የሆናችሁ ዜጎች አባል የሆናችሁበትን አደረጃጀት መታወቂያ ኮፒ እና የድጋፍ ደብዳቤ በማያያዝ ፎርም ሞልታችሁ ወደ ዳያስፖራ ክፍል በመቅረብ የድጋፍ ደብዳቤ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን። ነገር ግን ዳያስፖራ ክፍል የሚሰጠው ድጋፍ ደብዳቤ ድንበር ማሻገሪያ አይደለም።

7ኛ/ በማህበር ተደራጅታችሁ አገር ቤት መግባት የምትፈልጉ የአባላቱን ስም ዝርዝር የያዘ ማመልከቻ እና የእያንዳንዱን አባል መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ኮፒ በማያያዝ ወደ ዳያስፖራ ክፍል በመቅረብ የድጋፍ ደብዳቤ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን። ሰነድ የሌላቸው አባላት ካሉ ከላይ በተገለጸው መሠረት ወደ ቆንስላ ክፍላችን በመቅረብ ማመልከት ይጠበቅባቸዋል።

8ኛ/ የአገልግሎት ክፍያ ወይም ታሚን ጉዳይ ያላችሁ የሚመለከታቸውን የሱዳን መስሪያ ቤቶች እያነጋገርን ስለሆነ በትዕግስት እንድትጠብቁ እናሳስባለን።

9ኛ/ አዲስ መታወቂያ ሳያወጡ ወደ አገር መግባት አይቻልም በሚል በስፋት እየተነገረ ያለው ጥቂት ሙከራ ካልሆነ በስተቀር እስካሁን ወደ አገር ቤት ለመሄድ ወጥቶ የተመለሰ ዜጋ አለመኖሩን አረጋግጠናል። እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥም ወደ ኤምባሲያችን ደውላችሁ ማሳወቅ የምትችሉ መሆኑን እንጠቁማለን።

10ኛ/ ከጉሙሩክ ቀረጥ ጋር በተያያዘ አዲስ የወጣውን መመሪያ ለሁሉም ልማት ማህበራት አንዳንድ ኮፒ የተሰጠ በመሆኑ ከዚያ ላይ ወይም ከፌስ ቡክ ገጻችን ላይ መመልከት የሚቻል መሆኑን እንጠቁማለን። አዳዲስ ከኤሌክትሮኒክ ዕቃ ይዛችሁ መሄድ የምትፈልጉ የገዛችሁበትን ፋክቱር ከራሳችሁ እንዳይለይ እናሳስባለን።

በአጠቃላይ የዜጎች ጉዳይ አስመልክቶ ኤምባሲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን እንገልጻለን።

ከኢፌዴሪ ኤምባሲ ካርቱም
ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here